Announcement በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መካከል የሰልጣኞችን የስነ-ልቦና ደህንነት ለማረጋገጥ ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ ተገባ ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መካከል የሰልጣኞችን የስነ-ልቦና ደህንነት ለማረጋገጥ ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ ተገባ ።

13th July, 2026

ሰኔ 25/2018

የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችን አካዳሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጤንነት ለማረጋገጥ እና ድጋፉን ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት (MoU) በአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት የተፈረመ ሲሆን በዛሬው እለት የዩንቨርስቲው የሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት የ3ኛ ዓመት የኢንተርንሺፕ ተማሪዎች በኮሌጁ በመገኘት ስለ ኮሌጁ ገለጻና ጉብኘት አድርገዋል ።

ይህ ስትራቴጂካዊ የትብብር ማዕቀፍ የተዘረጋው በጀርመን ተራድኦ ድርጅት (GIZ-QEP II) ፕሮጀክት አስተባባሪነት ሲሆን ኮሌጁ ከሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ አንዱ የሆነው የሙያና ስነ-ልቦና ምክር (VGC) አገልግሎትን በሙያ ከማጠናከር አንጻር የሚኖረው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ተገልጿል።
በነበረው የተማሪዎች ስራ ማስጀመሪያ የውይይት መርሃ ግብር ላይ የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ፀጋዬ አዱኛ የተገኙ ሲሆን የመክፈቻ ንግግርም አድርገዋል ። በንግግራቸውም ኮሌጁ ከተመሰረተ ጀምሮ የመጣበትን ታሪካዊ ዳራውን በማንሳት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኮሌጁ እያስመዘገበ ያለውን ዘረፈ ብዙ ውጤት በማንሳት በቀጣይ የዚህ ኮሌጅ አባል በመሆን የተሻለ ስራ እንዲሰሩና በሙያቸው ኮሌጁን እንዲደግፉ በማሳሰብ በኮሌጁ የሚፈልጉትን ማነኛውም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በመግለጽ የእንኳን ደህና መጣቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈውል። የኮሌጁ የስልጠናና አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ዲን የሆኑት ወ/ሮ ፋንታዬ ባቡሎ በበኩላቸው በተደረገው የጋራ ስምምነት መደሰታቸውን ገልፀው በቀጣይ ከዩንቨርስቲው ጋር በጣም በቅርበት በመስራት የኮሌጁን ሰልጣኞች የስነ ልቦና እና የሞራል ግንባታ ስራዎች እንደሚሰራ ተናግረዋል ። ለዚህ ደግሞ እዚህ የተገኛቹ የዩንቨርስቲው ተማሪዎች ከኮሌጁ የVGC ባለሙያዎች ጋር በመሆን ባላችሁ ጊዜ ተናቦ መስራት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመርሃግብሩ ላይ የኮሌጁ የበላይ አ መራሮች ፣የGIZ አስተባባሪዎች፣ የGIZ የኪሌጁ አስተባባሪ፣የዩንቨርሲቲው ተወካይ፣የዩንቨርሲቲው የ3ኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ዲፓርትመንት ተማሪዎች እንዲሁም የኮሌጁ የሙያና ስነ-ልቦና ምክር (VGC) ቡድን ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን ጠቃሚ የሆኑ የሁለትዮሽ ውይይትና በኮሌጁ ጉብኘት በማድረግ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with